ከምንዛሪ ለውጡ ሦስት ወራት በኋላ ቢራ አምራቾች የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ጀመሩ

ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተደንግጎ ተግባራዊ የተደረገው በ15 በመቶ የምንዛሪ ለውጡን በመንተራስ የዋጋ ጭማሪ ካደረጉ በርካታ የንግድ ዘርፎችና አምራቾች ውስጥ የቢራ ፋብሪካዎች ይጠቀሳሉ፡፡

የቢራ ፋብሪካዎች የምንዛሪ ለውጡን በመከተል ያደረጉት የምርት መሸጫ ዋጋ ጭማሪ አግባብ እንዳልሆነ ተነግሯቸውና ሕዝብም እንዲያውቀው ተደርጎ፣ የብር የዋጋ ጭማሪውን በማንሳት እንደ ቀድሟቸው በነባሩ ዋጋ እንዲያመርቱ በመንግሥት መገደዳቸው ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ሁሉም ቢራ ፋብሪካዎች ከ12 እስከ 15 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አድርገው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከሦስት ወራት በላይ ያደረጉትን ጭማሪ አንስተው ከቆዩት ፋብሪካዎች መካከል ቢጂአይ ኢትዮጵያ የምርት ማከፋፈያ ዋጋው ላይ ጭማሪ በማድረግ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ሽያጭ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ሌሎቹም የቢራ ፋብሪካዎች በተመሳሳይ መንገድ ምርቶቻቸው ላይ ዋጋ በመጨመር ወደ ገበያ ለማስገባት ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ለአንዳንድ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን ለገበያ ከማዋል ሲታቀቡ እንደሚታዩ ተጠቃሚዎች ገልጸዋል፡፡

ከሰኞ ጥር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ቢጂአይ በምርቶቹ ላይ የዋጋ ጭማሪ አድርጎ መሸጥ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ በነበሩት ቀናት ውስጥ የፋብሪካው መጠጥ አከፋፋዮች፣ በማስረከቢያ ዋጋቸው ላይ ጭማሪ በማድረግ ሲሸጡ እንደነበር ተሰምቷል፡፡

የቢጂአይ ኢትዮጵያ ምርቶችን በማከፋፈያ ዋጋ ከሚረከቡ ሆቴሎችና ከሌሎችም የንግድ ተቋማት ባለቤቶች መረዳት እንደተቻለው፣ ከዚህ ቀደም በ214 ብር ይረከቡት የነበረው አንድ ሳጥን (24 ጠርሙስ የሚይዝ) ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ፣ ከዋጋ ጭማሪው በኋላ ግን በ251 ብር መረከብ እንደጀመሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ፋብሪካው በአንድ ሳጥን ቢራ ላይ የ37 ብር ጭማሪ ማድረጉን እንደሚያመላክት ነጋዴዎቹ ጠቅሰዋል፡፡

የቢጂአይ ምርት በሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ድራፍት ላይም በበርሜል የ110 ብር ጭማሪ እንደተደረገበት ነጋዴዎቹ ገልጸው፣ ፋብሪካው አንዱን በርሜል ድራፍት ቢራ ከዋጋ ጭማሪው በፊት በ590 ብር ይሸጥላቸው እንደነበር፣ በአዲሱ ዋጋ ግን በ700 ብር እንዲገዙ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ኃላፊዎች ስለዋጋ ጭማሪው እንዳረጋገጠው ከሆነ፣ የጭማሪው ምክንያት ከውጭ በሚገቡ ግብዓቶች ማለትም የብቅል ዋጋና ሌሎችም ምርቶች ላይ የምንዛሪ ለውጡ ያስከተለው የዋጋ ለውጥ በቢራ ምርቶች ዋጋ ላይ መንፀባረቅ በመጀመሩ የተፈጠረ የዋጋ ለውጥ ነው፡፡

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ምርቶች በስተቀር በተለይ በጥር 5 እና 6 ቀን 2010 ዓ.ም.  የሌሎች ቢራ ፋብሪካዎችን ምርቶች ማግኘት እንዳልቻሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሆቴል፣ የግሮሰሪና የሬስቶራንት ባለቤቶች ገልጸዋል፡፡ ምርቶቹ እንደወትሮው በሰፊው ለገበያ ያልወጡት የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ነጋዴዎቹ  ገልጸዋል፡፡

የቢራ ምርቶች ላይ ለተደረገው የዋጋ ለውጥ ዋነኛ ምክንያቱ የምንዛሪ ለውጡ እንደሆነ አብዛኞቹ አምራቾች የሚጠቅሱት ሲሆን፣ ለቢራ ምርት የሚስፈልጉና ከውጭ የሚገቡ እንደ ጌሾና ብቅል የመሳሰሉት ግብዓቶች በምንዛሪ ለውጡ ሰበብ ተጨማሪ ገንዘብ ስለሚጠይቁ ነው የሚለው መከራከሪያ እየቀረበ ነው፡፡ የብቅል ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ጭማሪ ማድረጉም ለዋጋ ለውጡ ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ እየቀረበ ነው፡፡ Reporter

Multilink Consulting