የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ስድስት በመቶ ዝቅ ያደረገ ትንበያ አስቀምጧል

የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በኮትዲቯር ዋና ከተማ አቢጃን ይፋ ያደረገው ሪፖርት፣ ከቃኛቸው አገሮች ውስጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም ተቃኝቷል፡፡

ባንኩ ‹‹አፍሪካን ኢኮኖሚክ አውትሉክ፣ 2018›› በሚል ርዕስ ይፋ ያደረገው ሪፖርት የአፍሪካ አገሮችን ኢኮኖሚያዊ ክንውን ከመዳሰስ ባሻገር በመጪዎቹ ዓመታት ማለትም እ.ኤ.አ. እስከ 2019 ሊታዩ የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ ትንበያዎችንም አስፍሯል፡፡

በአፍሪካ ልማት ባንክ ትንታኔ መሠረት፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ያሳየችው ዝቅተኛ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከድክመቶቿ ውስጥ የሚጠቀሰው ነው፡፡ የድርቅ ችግሮችና የወጣቶች ሥራ አጥነትም በባንኩ የአደጋ ሥጋት ከሚያንዣብባቸው ውስጥ ተመድበዋል፡፡ የወጪ ንግዱ ከገቢ ንግዱ አኳያ የ20 በመቶ ብቻ ሽፋን በመያዙ ወይም የገቢ ንግዱ ከወጪ ንግዱ ይልቅ ከፍተኛ የበላይነት በያዙ በአገሪቱ የንግድ ሚዛን ጉድለትን በማባባስና የውጭ ምንዛሪ እጥረትም እንዲባባስ ምክንያት መሆኑ ታይቷል፡፡ ይህ ደካማ አፈጻጸም የአገሪቱን የዕዳ ጫና ይበልጡን በወጪ ንግዱ ደካማ አፈጻጸም ሳቢያ ተጋላጭ እንዳደረገው ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

ይሁንና በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ብሎም መንግሥት በጥቅምት ወር ተግባራዊ የተደረገው የምንዛሪ ለውጥ የአገሪቱን የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከፍ እንደሚያደርጉት ተስፋ ተጥሏል፡፡ የማኑፋክቹሪንግ ዘርፉ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከሌሎች ምርቶች አኳያ የ20 በመቶ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል፡፡

ይህ ቢባልም የኢኮኖሚው ዕድገት ሊፈታቸው ከሚገቡ ችግሮች መካከል ትልቁን ሥጋት መደቀኑ የሚነገርለት የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር በአፍሪካ ልማት ባንክ ከተጠቆሙት ውስጥ ሆኗል፡፡ አከራካሪ መረጃ ቢሆንም የዕድሜ ክልላቸው ከ15 እስከ 29 ዓመት ከሆኑ ወጣቶች ውስጥ እስካለፈው አራት ዓመት ሥራ አጥ የሆኑት ሰባት በመቶ ብቻ እንደነበሩ ባንኩ አስታውሶ፣ ከእነዚህ መካከል ግን በከተማ የሚኖሩ ሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር ከ23 በመቶ በላይ መሆኑን፣ በዚህም ሳቢያ መንግሥት ከ10 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ወይም 500 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲመድብ ያስገደደው የሥራ አጥነት ችግር መከሰቱን የባንኩ ሪፖርት አስታውሷል፡፡ መንግሥት በአገሪቱ ወጣቶች ለተነሳው የፖለቲካ ቀውስ አንዱ መነሻ የሥራ አጥነት እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ ደጋግሞ የተከሰተው ድርቅ መንግሥት ተጨማሪ በጀት በመመደብ የእህል ግዥ እንዲፈጽም ማስገደዱንም ኢኮኖሚው ላይ የተጋረጠ ጫና እንደነበር የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት ጠቅሷል፡፡ እንዲህ ያሉ ጫናዎች እያደገ ከመጣው የብድር ዕዳ ጫና ጋር ተዳምረው አገሪቱ ስታስመዘግብ የነበረውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ግስጋሴ እየጎተቱ ስለመምጣታቸው የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት ይጠቅሳል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1977 ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት አገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ግስጋሴ ማሳየት ጀምራ ስትደናቀፍ የታየችባቸውን ጊዜያት በመጥቀስ፣ በቅርቡ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2014 ከተከሰተው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውሶች በማገገም ላይ እንደምትገኝም ጠቅሷል፡፡

እንዲህ ያሉት ክንውኖች የተስተናገዱበት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተሸኘው የምዕራባውያን ዓመት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በ6.8 በመቶ ማደጉን የጠቀሰው የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ዘንድሮና በመጪው ዓመትም በ6.9 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ትንበያውን አስፍሯል፡፡ በአንፃሩ ከሰሞኑ ይፋ የተደረጉ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ሪፖርቶች፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከስምንት በመቶ በላይ ዕድገት እንደሚያስመዘገብ መተንበያቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ያወጣው ሪፖርትም ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው የ8.3 በመቶ ዕድገት በዓለም ትልቁ በመሆኑ ቀዳሚነቱን ይዞ እንደነበር ማስነበቡ ይታወሳል፡፡

ይህም ሆኖ መንግሥት በአገሪቱ የበጀት ዘመን ማለትም በ2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት 11 በመቶ እንደሚያስመዘግብ ግምቱን አስታውቆ ነበር፡፡ መንግሥት ይህን ትንበያ ያስቀምጥ እንጂ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የኢኮኖሚው ዕድገት ከዘጠኝ በመቶ በታች ሲዋልል ከርሟል፡፡ የዓለም ባንክ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው ትንበያም ቢሆን፣ ኢኮኖሚው ከባለሁለት አኃዝ ዝቅ የሚል ዕድገት እንደሚኖረው አስፍሯል፡፡

የዓለም ባንክ ትንበያ የ8.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚኖር ይጠቅሳል፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅት በበኩሉ የ8.1 በመቶ ዕድገት አስፍሯል፡፡ ሌሎች ዓለም አቀፍ ትንበያዎችም ከ7.2 በመቶ እስከ 7.5 በመቶ እንደሚያድግ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ በተለይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥር 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኒውዮርክ ይፋ ያደረገው ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ. ከ2009 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ በየዓመቱ የተመዘገበውን ዕድገት ሲያስቀምጥ፣ በአዲሱ የምዕራባውያን ዓመት የ7.3 በመቶ፣ በመጪው ዓመትም የ7.5 በመቶ ዕድገት ዕድገት እንደሚመዘገብ አስፍሯል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ በተመድ የዓለም የንግድና የልማት ጉባዔን ጨምሮ በርካታ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የተሳተፉበት ይፋ የተመድ ሪፖርት፣ ላለፉት ሰባት ዓመታት በአማካይ የአሥር በመቶ ዕድገት ሲመዘገብ መቆየቱን በማስፈር በአሁኑ ዓመትና በመጪውም የሚኖረው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ግን ከሰባት በመቶ እንደማይበልጥ አትቷል፡፡

 የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምንም እንኳ በውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖች እየታሸም ቢሆን፣ በዚህ ዓመት እንደሚያስመዘግብ የሚጠበቀው ዕድገት ግን ከጋና ቀጥሎ በአፍሪካ ትልቁ ነው፡፡ ጋና ከኢትዮጵያ የበላይነቱ በመረከብ በአፍሪካ ትልቁን የኢኮኖሚ ዕድገት እንደምታስመዘገብ የሁለቱ ተቋማት ትንበያ ያሳያል፡፡

ምንም እንኳ አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ ጋና የምታስመዘገበው ዕድገት 8.3 በመቶ እንደሆነ ያስፍሩ እንጂ፣ የተመድ ትንበያ ግን የጋና ዕድገት በዚህ ዓመት ከሚያስመዘግበው የ7.5 በመቶ መጠን ወደ 5.9 በመቶ በመጪው ዓመት ዝቅ እንደሚል አስፍሯል፡፡ ከሁለቱ አገሮች በተጓዳኝ ሩዋንዳ የሰባት በመቶ ዕድገት እንምታስመዘግብ ሲገመት፣ ኬንያ፣ ታንዛንያና ኡጋንዳም በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የሚባለውን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያስተናግዱ አገሮች ተርታ ይመደባሉ፡፡

Multilink Consulting