አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እምብርት ናት፡፡ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ያላት ሚና ላቅ ያለ ከመሆኑም በላይ፣ የበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በመሆኗ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም ጭምር ተፈላጊ ናት፡፡ የአዲስ አበባ ነገር ሲነሳ ከዕድሜ ጠገብነቷና ከማዕከላዊ መንግሥት መቀመጫነቷ በዘለለ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ሥፍራ በወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ላይ ለመነጋገር ያነሳሳል፡፡ ‹‹አዲስ አበባ የማን ናት?›› የሚለውን የስግብግቦችና የራዕይ አልባዎች ንትርክ በመናቅ፣ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳትሆን የአፍሪካውያውያን ጭምር ስለሆነች ከተማ መጨነቅ ይገባል፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ ከጋይንትም ይምጣ ከጎዴ፣ ከክብረት መንግሥትም ይምጣ ከክልተ አውላሎ በማንም ገፋፊነት ሳይሆን በራሱ ፈቃድ ነዋሪ መሆን መብቱ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ አዲስ አበባ ውስጥ ለመኖር የሚያስችለው ሥራና አቅም መኖሩን ማመዛዘን ያለበት ባለቤቱ መሆኑ መታመኑ ላይ ነው፡፡ እንዲሁም አዲስ አበባን ለመምራት ደግሞ አቅም፣ ብቃትና ሥነ ምግባር ያስፈልጋል፡፡ የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የኃላፊነት መርህም ሊኖር ይገባል፡፡ በነዋሪዎች መልካም ፈቃድ የሚመረጥ አመራርም መኖር አለበት፡፡ ከተማን ለመምራት የከተሜነትን ሥነ ልቦና መላበስም የግድ ይላል፡፡ በቅኝ ገዥዎች ሳይሆን በልጆቿ የተመሠረተች ብቸኛዋ የአፍሪካ ከተማ መዘመን ይገባታል፡፡
ከዚህ ቀደም ኢሕአዴግ አሁን ደግሞ ብልፅግና ፓርቲ በገዥ ፓርቲነታቸው የከተማዋን ቻርተር በአዋጅ እያሻሻሉ፣ የምክር ቤት አባል ያልሆኑ ከንቲባዎችን እያፈራረቁ እየሰየሙ ነው፡፡ ሰሞኑንም የቀድሞው ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በሌላ ሹመት ሲሰናበቱ፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የነበሩት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተተክተዋል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ጫና ሲቀንስ ይካሄዳል ተብሎ ተስፋ በሚደረገው በመጪው ምርጫ፣ በሕዝብ ድምፅ የሚመረጥ አመራር እስኪመጣ ድረስ ይህ አሠራር በዚህ ከመቀጠል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም ያለፈውን እያነሱ ስለወደፊቱ መነጋገር የግድ ይሆናል፡፡ ባለፉት 29 ዓመታት የከተማው አስተዳደር በኢሕአዴግ ድርጅቶች በፈረቃ ሲመራ፣ አንድም ጊዜ ማለት ይቻላል ከተማው ውስጥ ተወልዶ ያደገ ከንቲባ አልተሰየመም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ በአቶ አርከበ ዕቁባይና በአቶ ታከለ ኡማ ጊዜ በተነፃፃሪ የተሻለ አመራር አገኘ ቢባልም፣ ከአዲስ አበባ ዘርፈ ብዙ ችግሮች አኳያ እሮሮና ብሶቱ አልተነካም ማለት ይቻላል፡፡ እንዲያውም በአቶ ታከለ ጊዜ ከነዋሪዎች ጋር የተሻለ መቀራረብ በመፍጠር፣ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ሥራዎች መከናወናቸው የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ አዲስ አበባ የፖለቲካ ቅራኔ ዋሻ መሆኗም አይዘነጋም፡፡ ቅራኔው ደግሞ ብዙ አዳርሷል፡፡
አዲስ አበባ ግዙፍና ዘመናዊ ከተማ የሚያደርጋትን ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመንደፍ ይልቅ፣ በባለቤትነትና በይገባኛል ስሜት የሚስተዋለው መጠዛጠዝ ከተሜነትን የማይወክል ንፉግነትና ክፋት የተጠናወተው ነው፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ‹‹ሰፋሪ›› እያሉ የመኖርና የመሥራት ሁለንተናዊ መብትን የሚጋፉ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ገብቶ መኖርና መሥራት የሚፈልግ ኢትዮጵያዊን ‹‹ወራሪ›› አድርገው የሚቆጥሩ ጠባቦች የሚያመላክቱት የአገሪቱን ፖለቲካ መበላሸት ነው፡፡ እንኳንስ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ድርጅታቸውን በአዲስ አበባ የመሠረቱት አፍሪካውያን፣ እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶቻቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ጭምር ከተማዋ ቤታቸው ናት፡፡ ከትልልቆቹ የዓለም ከተሞች ተርታ ተሠልፋ ስሟ የሚጠራው አዲስ አበባ በፀጥታና ደኅንነት፣ በንፅህና፣ በዘመናዊ መንገዶችና በትራፊክ ማኔጅመንት፣ በባቡር ትራንስፖርት፣ በቴሌኮምና ተያያዥ አገልግሎቶች፣ በኤሌክትሪክና በንፁህ ውኃ አቅርቦት፣ በመናፈሻዎችና ፓርኮች፣ በዘመናዊ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች፣ ወዘተ ማደግ መመንደግ አለባት፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘመኑን የዋጀ ብቁ አመራር ያስፈልጋል፡፡ አመራሩ በነዋሪዎች በዕውቀቱ፣ በልምዱ፣ በሥነ ምግባሩና በማኅበራዊ ግንኙነቱ የተመሰከረለት ሊሆን ይገባል፡፡ አዲስ አበባ ከተማን በፖለቲካ ሥምሪት መነጽር ብቻ እየተመሩ፣ የብሔርና መሰል ግንኙነቶች መሰባሰቢያ የሚያደርግና ዝርፊያን የሚያበረታታ አሠራር መወገድ አለበት፡፡ አዲስ አበባ ዓለም አቀፋዊ ከተማ ስለሆነች አስተሳሰብን የላቀ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ችግር ብቻ ተሸክመው የሚኖሩ አይደሉም፡፡ በየክፍለ ከተማውና በየወረዳው የታጨቁ ችግር የማይፈቱ አመራሮችን የተሸከሙ ነዋሪዎች ዕድሉ ቢሰጣቸው፣ አንፀባራቂ ተግባራት ማከናወን የሚችሉ የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የሆኑ የተካኑ ግለሰቦችን ነቅሰው ማውጣት ይችላሉ፡፡ አዲስ አበባ በመልካም አስተዳደር አልታደለችም፡፡ አሁንም ሆነ በፊት ከማዕከል ጀምሮ በክፍላተ ከተሞችም ሆነ በወረዳዎች ውስጥ ካሉ አመራሮች አብዛኞቹ ነዋሪውን መቅረብ የማይፈልጉ፣ በራሳቸው የማይተማመኑ፣ የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው፣ ለያዙት ኃላፊነት የማይመጥኑ፣ ከተሜነትን ያልተላበሱ፣ ወዘተ ለመሆናቸው ከነዋሪዎች በላይ ምስክር የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከወረዳ ጀምሮ ደንብ አስከባሪዎችን በሚገባ አሰማርተው ነዋሪዎችን ከነጣቂዎችና ከዘራፊዎች መከላከል የማይችሉ ናቸው፡፡ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ በአግባቡ ማስወገድ የተሳናቸው ናቸው፡፡ ከኪስ አውላቂዎች እስከ መሬት ወራሪዎች ድረስ ከኅብረተሰቡ ጥቆማ እየቀረበላቸው፣ የጥቅም ተባባሪ ይመስል ምላሽ መስጠት የተሳናቸው ናቸው፡፡ ደንብ አስከባሪዎችን ከፖሊስ ጋር አቀናጅተው ወንጀል ለመከላከል ባለመቻላቸው፣ አዲስ አበባ የወንበዴዎች ዋሻ እየሆነች ነው፡፡ የነዋሪዎችን አመኔታ ያተረፈ ንቁና ብቁ አመራር የሚያስፈልገው ለእነዚህ ጉዳዮች ጭምር ነው፡፡
አዲስ አበባን አንዴ ‹‹ፊንፊኔ››፣ አንዴ ‹‹በረራ›› እያሉ በባለቤትነት ሽሚያ ኢትዮጵያዊያንን ግራ የሚያጋቡ ፖለቲከኞችም ሆኑ ተከታዮቻቸው፣ በመጀመርያ የአገሪቱ ብቻ ሳትሆን የዓለም መናኸሪያ የሆነችውን ከተማ በዘመናዊ የአስተሳሰብ ዓውድ ውስጥ ሆነው ለመመልከት ጥረት ያድርጉ፡፡ በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሳሪ አስተሳሰብ ተላቆ፣ ከተማዋ የበለጠ አብባና ጎምርታ ለነዋሪዎቿ የተመቸችና የቱሪስቶች መስህብ እንድትሆን ዘመናዊ አስተሳሰብ ይላበስ፡፡ ከእንጦጦ ጀምሮ እስከ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ድረስ የሚዘልቀውና መስቀል አደባባይን የሚያዳርሰው ፕሮጀክት፣ አዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የያዘው ትልም በከፍተኛ ደረጃ የሚደገፍ ነው፡፡ አሁን ያለውን ጅምር በተሳካ ሁኔታ ከግብ ለማድረስ ግን ከቀድሞዎቹ የላቀ አስተሳሰብ፣ ብቃትና ልምድ ያላቸውን በወረንጦ መፈለግ የግድ ይሆናል፡፡ የወደፊቱ የከተማ አስተዳደር አመራር አሰያየም እንዴት መሆን አለበት ከሚለው ዕይታ በመጀመር፣ አዲስ አበባን በየዕለቱ የለውጥ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ተቋማዊ ሥርዓት ማበጀት ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ ግለሰባዊ ተክለ ሰብዕና ላይ የተመሠረተ አስተዳደር ለብልሹ አሠራሮች ከመዳረጉም በላይ፣ ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ በማድረግ ለቅራኔ በር ይከፍታል፡፡ በተጨማሪም በገዥው ፓርቲ ውስጥ የተለመደውን ድርጅታዊ ሽኩቻ በመቀስቀስ፣ ለሰላምና ለመረጋጋት ጠንቅ ይሆናል፡፡
አዲሷ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ በመሆናቸው፣ እስከ መጪው ምርጫ ድረስ በሚኖራቸው ቆይታ የከተማዋን ዋና ዋና ችግሮች ቢያስተውሉ መልካም ነው፡፡ ከተማዋ ውስጥ መጠኑን ለመግለጽ የሚያዳግት ድህነት መኖሩን አይስቱትም፡፡ የኑሮ ውድነት እንደ እሳት የሚገርፋቸው ነዋሪዎች ገበያው እንዲረጋጋላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የሚታወቁት የውኃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የትራንስፖርትና ሌሎች ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች መስተጓጎል አሁንም ብርቱ ጥያቄዎች ይነሳባቸዋል፡፡ በክፍለ ከተማም ሆነ በወረዳ ጉዳይን በቶሎ አለመፈጸምና ጉቦ ነዋሪዎችን እያማረረ ነው፡፡ የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር፣ የወንጀል መበራከትና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጉዳይም ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ በመኖሪያ ቤት ችግር የሚሰቃዩ ነዋሪዎች ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ትኩረት ይሻል፡፡ በተጨማሪም ለተቋማት ግንባታና ጥንካሬ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሌላው አደገኛውና አስነዋሪው ድርጊት የመሬት ወረራ ነው፡፡ በአደገኛ ደላሎች ጉዳይ ፈጻሚዎች አቀናባሪነትና በፖለቲከኞች ፊታውራሪነት የሚከናወነው ይህ የመሬት ወረራ፣ በአገሩ መንግሥት የለም ወይ ከማስባልም በላይ የዘለለ ነው፡፡ ከተማዋ ባለቤት የሌላት ይመስል በአንዳንድ የኮንዶሚኒየም ግቢዎች ውስጥ ጭምር መሬት በጉልበተኞች እየታጠረ ነው፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሔው ሕግና ሥርዓት ማስከበር ብቻ ነው፡፡ ከሕግ በላይ የሆኑ ጉልበተኞች በፍጥነት በሕግ አደብ ይግዙ፡፡ አዲሷ ምክትል ከንቲባ ይህ ሁሉ ጉድ ይጠፋቸዋል ተብሎ ባይታሰብም ለግልጽነት፣ ለተጠያቂነትና ለኃላፊነት ትኩረት ይስጡ፡፡ የአዲስ አበባ ነገር ብዙ ቢያነጋግርም ለጊዜው ከብዙ በጥቂቱ ይህንን ይመስላል!
Source: Reporter